በደቡብ ሪጅን በሚገኙ 12 ከተሞች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት በይፋ ተጀመረ


ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) –
ሀዋሳ ከተማ ጨምሮ በደቡብ ሪጅን በሚገኙ 12 ከተሞች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት በይፋ ተጀመረ።
የ4ጂ አገልግሎት የላቀ ፍጥነትና አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ደንበኞች የተሻለ አገልግልት ማግኘች እንደሚችሉ ነው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ የተናገሩት።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አገልግሎቱ ምርታማነትን ለማሳደግ እና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የዜጎች የኢንተርኔት አጠቃቀም ሁኔታ እያደገ መጥቷል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አሁን ላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 25 ነጥብ 3 ሚሊየን መድረሱን ገልፀዋል።
አጠቃላይ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር 55 ነጥብ 4 ሚሊየን ደርሷልም ነው ያሉት።
በዛሬው ዕለት በ12 ከተሞች አገልግልት መስጠት የጀመረው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ ከ9 መቶ ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
የዛሬውን ሳይጨምር በአዲስ አበባ ፣ በደቡብ ምሥራቅ ሪጅን፣ በሰሜን ምዕራብ ሪጅን፣ በምሥራቅ ምሥራቅ ሪጅን፣ በደቡብ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን፣ በምስራቅ ሪጅን፣ በማዕከላዊ ምስራቅ ሪጅን ፣ በሰሜን ምስራቅ ሪጅን እና በሰሜን ምሥራቅ ምሥራቅ ሪጅን የሚገኙ 53 ከተሞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
(በበሃይሉ ጌታቸው)