በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ በተከሰተ ግጭት ከ9 ሺሕ 500 በላይ ዜጎች ተፈናቀሉ

መጋቢት 4/2014 (ዋልታ) በጋምቤላና በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ በተከሰተ የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት በጋምቤላ ክልል ከ9 ሺሕ 500 በላይ የላሬና የጂካዎ ወረዳ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

በግጭቱ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ተፈናቃዮች በኑዌር ዞን በላሬና በጂካዎ ወረዳዎች ሥር የሚገኙ የአራት ቀበሌ ነዋሪዎች መሆናቸውም ተመልክቷል።

የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡገቱ አዲንግ በደቡብ ሱዳን የኤስ ፒ ኤል ኤም-ኤልኦ ወታደሮችና በደቡብ ሱዳን መንግሥት መካከል ሰሞኑን ግጭት መከሰቱን ተናግረዋል፡፡

በተከሰተው ግጭት ምክንያት ከ9 ሺሕ 500 በላይ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።