በደቡብ አፍሪካ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አስቀድሞ የታቀደ እንደነበር ተገለጸ

ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – የቀድሞውን ፕሬዝዳንት መታሰር ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የተቀሰቀሰው ተቃውሞና አመጽ አስቀድሞ የታቀደ እንደነበር ማረጋገጣቸውን ሀአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቱ ተቃውሞው የተቀሰቀሳባትን የመጀመሪያ ግዛት ኩዋዙሉ ናታልን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት በደቡብ አፍሪካ የተቀሰቀሰው ተቃውሞና አመጽ ዴሞክራሲ ላይ የተፈጸመ አሻጥር ነው።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ተቃውሞውና አመጹ ቀድሞ የታቀደ መሆኑን በምርመራ አረጋግጠናል ይህም የዴሞክራሲን ተግባራዊነት እና የህግን የበላይነት ለማረጋገጥ የምናካሂደውን እንቅስቃሴ ለመግታት ቅድመ ዝግጀት ተደርጎበት የተተገበረ ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ድርጊቱን ያቀነባበሩት ማንነት ለይተው እየተከታተሏቸው መሆኑን ገልጸው የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ሂደት የሚያደናቅፉትንም እንደማይታገሱ አሳስበዋል።

ከ212 በላይ ሰዎች በአመጹ መሞታቸውም ሲነገር ከ2ሺ 500 በላይ ሰዎች ደግሞ ከአመጹ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሀገሪቱ  ፖሊስ አስታውቋል።

በደቡብ አፍሪካ ሳምንት ባስቆጠረው አመጽ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች የወደሙ ሲሆን፤ የንግድ ተቋማት የዘረፋና የቃጠሎ አደጋ እንደደረሰባቸው ተነግሯል፡፡