በደቡብ ክልል በ2015 አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ትግበራ እንደሚጀመር ተገለጸ

ሐምሌ 26/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል በ2015 የትምህርት ዘመን አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ትግበራ እንደሚጀመር የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ በ2015 የትምህርት ዓመት እቅድ ዋና ዋና የትኩረት መስኮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) እንደገለጹት በ2015 የትምህርት ዘመን በክልሉ አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ትግበራ ሙሉ ለሙሉ ይጀመራል።

የትምህርቱን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ የተቀረጸው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በክልሉ ባሳለፍነው ዓመት በሙከራ ደረጃ መጀመሩን አስታውሰው በ2015 ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚሸጋገር ጠቁመዋል።

የፖለቲካ አመራሩ እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የክልሉን የትምህርት ገጽታ ለመቀየር የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በውይይት መድረኩ ከክልል እና ከከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።