በደቡብ ወሎ 358 የአሸባሪው ታጣቂዎች መያዝ

ጳጉሜ 4/2013 (ዋልታ) በደቡብ ወሎ ዞን 358 የአሸባሪው ሕወሓት ሰርጎ ገብ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሰይድ መሀመድ በዞኑ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም የሕወሓት አሸባሪ ቡድን አባላት በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ሰርገው በመግባት ጥፋት ለመፈፀም ያደረጉት ጥረት በአካባቢው ማኅበረሰብ ንቃት ከሽፏል ብለዋል።

በተለይም ወጣቶች አካባቢያቸውን ሌት ተቀን በንቃት በመጠበቃቸው 358 የሽብር ቡድኑ ሰርጎ ገቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የገለፁት።

አሸባሪው ሕወሓት በተለይም “የአማራን ሕዝብ እረፍት እነሳለሁ ኢትዮጵያንም አፈርሳለሁ” ብሎ ተነስቷል ሲሉ ያስታወሱት ዋና አስተዳዳሪው በዓሉን ሽፋን አድርጎ ሽብር ለመፍጠር እየሞከረ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም የዞኑ ሕዝብ በዓሉን ሲያከብር ሰላሙን በመጠበቅ “ፀጉረ ልውጦችን” በንቃት መከታተል አለበት ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ የግለሰብ፣ የሕዝብና የመንግሥት ተቋማትን ዘርፎ ለመውሰድ በአካባቢው 400 በላይ ተሽከርካሪዎችን አሰማርቶ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
የሽብር ቡድኑን አረመኔነት የተረዳው የወሎ ወጣት፣ ሚሊሻው እንዲሁም አርሶ አደሩ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን መፋለማቸውን ተናግረዋል።

100 ብር ለወገኔ በሚል የድጋፍ ማሰባሰቢያ በዞኑ ለአገር ኅልውና ዘመቻው ከ151 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሃብት በዓይነትና በገንዘብ መሰበሰቡንም አክለዋል።
በሳራ ስዩም