በደገሀቡር እና ጅግጅጋ ሪፈራል ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ያገባኛል ኢኒሼቲቭ ተጀመረ

ሚያዝያ 05/2013 (ዋልታ) – በሶማሌ ክልል በደገሀቡር ሆስፒታል እና በጅግጅጋ ሪፈራል የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ጥራትን፣ ፍትሀዊነትን እና ተደራሽነትን እንደሚያሻሽል የታመነበት ያገባኛል (I CARE) የተሰኘው ኢኒሼቲቭ በይፋ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በሀገሪቱ የህክምና ተቋማት የህክምና አገልግሎት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ያገባኛል የተሰኘው ኢኒሼቲቭ ጥራትን፣ ፍትሀዊነትን፣ ተደራሽነትን እና ሌሎች በህክምና ተቋማት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አንዱ ኢኒሼቲቭ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል እና በደገሀቡር ሆስፒታል ጥራትን፣ ፍትሀዊነትን እና ተደራሽነትን ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በማገዝ ረገድ ያገባኛል የተሰኘው ኢኒሼቲቭ በአግባቡ መተግበር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ በደገሀቡር እና በጅግጅጋ ሪፈራል ሆስፒታሎች ተዘዋውረው ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በሆስፒታሎቹ የሚታዩ የህክምና መሳሪያዎች፣ የደም ባንክ አገልግሎት፣ የመድሀኒት እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በደገሀቡር ሆስፒታል ለዘመናዊ የፋርማሲ አገልግሎት የተሰራውን ህንጻም መርቀው ያስጀመሩ ሲሆን፣ እየተገነቡ ያሉ ማስፋፊያዎች ያሉበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡
በመርሀግብሩ ላይ የጤና ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች፣ የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ የስራ ሀላፊዎች፣ የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የስራ ሃላፊዎች፣ የደም ባንክና የተቋማቱ ሰራተኞች መገኘታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።