በዱባይ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አውደ-ርዕይ ላይ የተሠማሩ አምስት የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ

ነሐሴ 26/2014 (ዋልታ) በመጪው ህዳር ወር በዱባይ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አውደ-ርዕይ በቢዝነስ አውት ሶርሲንግ ላይ የተሠማሩ አምስት የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በመጪው ጥቅምት በዱባይ በሚካሄደው የጂአይቴክስ ግሎባል ኮንፈረንስ ላይ ከሚሳተፉ ኩባንያዎች ጋር ተወያይተዋል።

ኩባንያዎቹ የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የንግድ ማእከል በኮንፈረንሱ የሚሳተፉትን የቢፒኦ (ቢዝነስ ፕሮሰስ አውትሶርሲንግ) ኩባንያዎችን ለመምረጥ ማስታወቂያ አውጥቶ ካመለከቱት ውስጥ የተመረጡ ናቸው።

ኩባንያዎቹ አፍሪኮም ቴክኖሎጂዎች፣ ኤክስለረንት ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ፣ አይ ኔትወርክ ሶሉሽንስ፣ ኦርቢት ሄልዝ ሶሉሽንስ እና አርኤንዲዲ ግሩፕ ናቸው፡፡

ኮንፈረንሱ ለ41 ዓመታት የተካሄደ ሲሆን ዋና ዋና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላትን በተለይም ስማርት ከተሞችን፣ የሳይበር ደህንነትን፣ የመረጃ ኢኮኖሚን፣ ተንቀሳቃሽነትን፣ ዲጂታል ጤና አጠባበቅን እና ቴሌኮም ላይ በማተኮር ከ100 ሺሕ በላይ አለምአቀፍ ጎብኚዎችን፣ ከ4 ሺሕ በላይ የቴክኖሎጂ መሪዎችን እና 170 አገሮች የሚሳተፉበት ነው።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ኩባንያዎቹ የሚሳተፉት ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ለሌሎች ለማስተዋወቅ ጭምር መሆኑን ተገንዝበው ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደረጉ አሳስበዋል።

የቢዝንስ አውትሶርሲንግ ስራ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቲጂ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሚኒስቴሩ ኩባኒያዎቹ ለሚያደርጉት ዝግጅት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ያሉባት የወጣት አገር ከመሆኗም በላይ ባላት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥም ለቢዝነስ አውትሶርሲንግ የተመቸች አገር ብትሆንም እስካሁን ሳትጠቀመብት ቆይታለች።

ከዚህ ዘርፍ በአፍሪካ ናይጄሪያ እና ኬንያ የበለጠ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።