በዳውሮ ዞን ለሃገር መከላከያ ሠራዊት ከ11 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መሰብሰቡ ተገለፀ

ነሃሴ 20/2013 (ዋልታ) – በዳውሮ ዞን ለሃገር መከላከያ ሠራዊት ከ11 ሚሊዮን 17ሺህ 161 ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መሰብሰቡ ተገለፀ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ በዛብህ ከሁሉም የወረዳ መዋቅሮችና ታርጫ ከተማ አስተዳደር ማህበራዊ መሰረት አስር ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰላሳ አምስት ሽህ ዘጠኝ መቶ አስር ብር በላይ የሚገመት ሃብት በዛሬዉ ቀን ብቻ መሰብሰቡን ገልፀዋል።

የዳዉሮ ህዝብ ከአራት መቶ አመት በፊት ታላቁን ሃላላ የጦር መከላከያ ግንብ ከጥቁር ድንጋይ የገነባ ጦረኛ ህዝብ መሆኑን ያስታወሱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፣ በዛሬዉ ቀን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላደረጉት የሃብትና የሞራል ድጋፍ አመስግነዋል።

ዋና አስተዳዳሪዉ አክለዉም ጠላት ኢትዮጵያን እናፈርሳለን ካለ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸዉ ጎልቶና ጠንክሮ 6ኛ ዙር ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ድሞክራስያዊ በሆነ ሁኔታ በማካሄድና ሁለተኛዉን ዙር የህዳሴ ግድብ በመሙላት የኢትዮጵያን ብልፅግና ጉዞ ማደናቀፍ እንደማይቻል ማረጋገጣቸዉን አስታዉሰዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለየትኛዉም ጠላት እጅ ሰጥታ የማታዉቅ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት መሆኗን ያስታወሱት ዋና አስተዳዳሪዉ በዘመናችን የተከሰቱ የዉጭ ባዳዎችና የዉስጥ ባንዳዎች ደካማና ተላላኪ መንግስት ለመመስረት የሚያደርጉትን ሴራ የዞኑ ህዝብም እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እምቢ በማለትና የሃገር መከላከያ ሰራዊት በሃብትና በሞራል ለመደገፍ እያደረገ ያለዉ አንድነት የአሸናፊነት መገለጫ መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ ዋና ከተማ በሚገኘዉ ታርጫ ስታዲየም በዛሬዉ ቀን ብቻ ቀድመዉ ርክብክብ የተደረጉት 169 በሬ፣ 6 ፍዬል፣ 7 በግ፣ 13 ኩንታል ኩኪስ፣ 19 ኩንታል በሶ፣ 8 ኩንታል በቆሎ፣ 13 ኩንታል ጤፍ፣ 259 ኪሎ ግራም ቅቤ እና ሁለት ሚሊዮን ጥሬ ብር ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ መላኩን የሃብት አሰባሰብ ኮሚቴ ገልጿል።

በታርጫ ስታድዬም በተደረገዉ የሃብት አሰባሰብ መርሃ ግብር በክብር የተሰናበቱ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የሰልፍና የኪነጥበብ ሥራዎችን ያቀረቡ ስሆን 27 ዓመት ሃገሪቱን የዘረፋት አሸባሪዉ ህወሃት በሴሜን ኢዝና በማይካድራ የፈፀማቸዉ ግፎች የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ያጠናከረ ስለመሆኑ እንድሁም አሸባሪዉ ህወሃትና ኦኔግ ሽኔ ለመጨረሻ ጊዜ የሚደመሰሱበት ትክክለኛ ጊዜ መድረሱንንና መሰል መልዕክቶችን አስታዉሰዋል።

የዞኑ የሃብት አሰባሰብ ኮሚቴዉ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መግለጹን ከዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መመሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።