መጋቢት 27/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ቆላማ አካባቢዎች የተከሰተውን አስከፊ የምግብ እጥረት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ መንግሥት ገለጸ።
በክልሉ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር የተመራው የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ጠይቀዋል።
ችግሩ በተከሰተበት በዳውሮ ዞን ዛባ ጋዞ ወረዳ በጋራዳ እንታላና በጋራዳ ባጭሪ ቀበሌ ተገኝተው ተጎጂዎችን የጠየቁት የክልሉ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ/ር) ከዞንና ከአከባቢው አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር ለተከሰተው አስከፊ የምግብ እጥረት ችግር ጊዜያዊ መፍትሄ እየተሰጠ መሆኑን ገልፀው በዘላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ዝናብ በጊዜ ባለመዝነቡ ምክንያት አከባቢ ምርት እየሰጠ አይደለም ያሉት ርዕሠ መስተዳድሩ በአከባቢው በተከሰተው የአየር መዛባት መንስኤ በተከሰተው ድርቅ በርካታ ከብቶች እንደሞቱና በርካታ ሰዎች ለምግብ እጥረት እንደተጋለጡ አብራርተዋል።
በልዑካን ቡድኑ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው እንዲሁም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አልማው ዘውዴና ለሎች ከፍተኛ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቻን የዳውሮ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።