በድሬዳዋ በአንድ ጀምበር 500 ሺህ ችግኞች ተተከሉ


ድሬዳዋ ፣ ሐምሌ 29/2013 (ዋልታ) –
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በዛሬው ዕለት 500 ሺህ የደንና የጥምር ችግኞች በከተማና በገጠር ተተከሉ፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የግብርና ፣ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም የሱፍ በዘንድሮው የክረምት ወቅት 2 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል መታቀዱን አንስተዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድቡህ በበኩላቸው ኢትዮጵያን እናልብሳት መርሃ ግብር የሚተከሉት ችግኞች የጥምር ደንና ከተማ ማስዋቢያ ናቸው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ስራው በከተማዋ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና ስላለው ለድሬዳዋ ከተማ ልዩ ትርጉም አለው ያሉት ከንቲባው ችግኞች እንዲፀድቅ የጥበቃና የእንክብካቤ ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በረኛ ተካበ ዘውዴ በበኩላቸው የስፖርት ቤተሰቡ አረንጓዴ አሻራ ላይ በመሳተፍ ለሀገር ሰላም እና አብሮነት የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደ አንድ አጀንዳ በማድረግ የችግኝ ተከላ ስራው ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ የተናገሩት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ውባህ ሀሰን ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ ስላልሆነ መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
(በመማር ይበልጣል)