#ሕግ_ይዳኘኝ
የራስ ያልሆነን ገንዘብ መጠቀም ወይም በሌላ ሰው ሀብት ያለአግባብ መገልገል ለህሊና እዳ በሕጉም ቅጣትን የሚያስከትል ድርጊት ነው። ይሁን እንጂ ብዙዎች የራሳቸው ያልሆነን ንብረት በድፍረት ለመጠቀም ተኝተው አያድሩም።
እነዚህን ሰዎች በተመለከተ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ላይ በግልጽ ሕጋዊ ቅጣት ተቀምጧል። በዛሬው “ሕግ ይዳኘኝ” መረኃ ግብራችን ይህንኑ ጉዳይ እንዳስሰዋለን።
በሰው ሀብት ንብረት ያለአግባብ መጠቀም ከየትኛውም ሃይማኖታዊ አስተምህሮም ሆነ ከህሊና የራቀ መጥፎ ልማድ እና ተግባር ነው።
በኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 678 መሰረት ማንም ሰው ራሱን ወይም ሌላውን ሰው ያለአግባብ ለማበልጸግ በማሰብ፣ የንብረቱ ባለቤት በመብቱ እንዳይጠቀምበት ለማድረግ፣ በማታለል ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለጊዜው መጠቀሚያ ለማድረግ የሌላውን ሰው ንብረት የወሰደ እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከአምስት ሺሕ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል።
ማንም ሰው የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላ ሰው ንብረት ሆኖ በስህተት፣ ባልታሰብ ድንገተኛ አጋጣሚ ነገር፣ እንደ ውሃ ማዕበልና እንደነፋስ ባለ የተፈጥሮ ጠባይ በመጣ ኃይል ወይም ከባለቤቱ ፈቃድ ውጭ በሆነ በማናቸውም ሌላ ዓይነት ሁኔታ ከባለቤቱ እጅ ወጥቶ በእጁ የሚገኘውን ነገር (እቃ) ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ያደረገ እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በቀላል እስራት ወይም መቀጮ እንደሚቀጣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 679 ላይ ተደንግጓል።
በብርሃኑ አበራ