ከተፈጥሮ ሳንታረቅ ድህነትን ማሸነፍ አይቻልም – ምክትል ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

መጋቢት 20/2016 (አዲስ ዋልታ) የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ለዜጎች ንፁህና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር ያለመ ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅር እንዳሉት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠርና ድህነትን ለመዋጋት ከተፈጥሮ ጋር መታረቅ ወሳኝ በመሆኑ በዘርፉ ባለፉት አራት ዓመታት በስፋት በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።

አካባቢን ከብክለት ከመከላከል ባሻገር አረንጓዴ አሻራን ላይ በስፋት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

“ብክለት ይብቃ፤ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው መርኃ ግብሩ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከዩ ኤን ዲፒ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን የአካባቢ ብክለትና ተዛማጅ ችግሮችን በመቅረፍ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ለስድስት ወራት በሚቆየው ንቅናቄ የፕላስቲክ ብክለት፣ የአየር፣ የውሀና የድምፅ ብክለትን መከላከል የሚያስችል ተግባር ለማከናወን መታቀዱም በመርኃ ግብሩ ላይ ተጠቁሟል።

ለዚህ ደግሞ ሁሉም አካላት በጋራ በመሳተፍ ለትውልዱ ያማረና የበለፀገች ሀገርን ማስረከብ ይጠበቃል ተብሏል።

በንቅናቄው ከተሞችን ከፕላስቲክ ብክለት ነፃ ማድርግ፣ የእርሻ መሬቶችን ከአፈር አሲዳማነት መከላከል፣ የኢንዱስትሪዎች የኬሚካል አጠቃቀምን ማስተካከልና የአካባቢ ብክለትን መቆጣጠር የመሰሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተነግሯል።

በመድረኩ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር ጀነራል ለሊሴ ነሚን ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በብሩክታይት አፈሩ