የጅማ ከተማን ለሁለት አቋርጦ የሚያልፈው የአዌቱ ወንዝ ዳርቻን ለማልማት የ600 ሚሊየን ብር የውል ስምምነት ተፈረመ ።
የወንዝ ዳር ልማቱን በሚያከናውኑ በሳኢ መሀመድ፣ ሙስጠፋ ጀማልና ጥላሁን አበበ በተባሉ ሶስት የግንባታ ተቋራጮች የስራው ባለቤት ከሆነው የጅማ ከተማ አስተዳደር ጋር የውል ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
የጅማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ከድር ሀሰን ለኢዜአ እንደገለጹት የአዌቱ ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የግንባታ ስራ በሶስት ስራ ተቋራጮች የሚገነባ ነው።
የወንዝ ዳርጃ ልማት ፕሮጀክቱ በከተማው አስተዳደር በሚመደብ በጀትና በዓለም ባንክ ገንዘብ ድጋፍ በሶስት የሥራ ደረጃዎች ተከፋፍሎ የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
የመጀመሪያው የፕሮጀክት ስራ በ101 ሚሊዮን ብር በጀት የሚከናወንና በአስራ አንድ ወር ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ቀሪዎቹ ሁለት ፕሮጀክቶች በ499 ሚሊዮን ብር በጀት በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚከናወኑ የገለጹት ስራ አስኪያጁ አጠቃላይ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቱ በሶስት አመት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመጀመሪያው ፕሮጀክት ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል የአዌቱ የህዝብ መናፈሻን ከትንሿ ስታዲዬም የሚያገናኝ ድልድይ እንዲሁም የወጣቶች ማዕከል ግንባታ ያካለለ ልማት እንደሚካሄድ ለአብነት ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ የውሃ ማጣሪያ፣ የተለያዩ ድልድዮች፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ መጽሃፍት ቤቶች፣ የወጣቶች መዝናኛዎችና የተለያዩ የገበያ ማዕከሎችን በውስጡ ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።