ሰኔ 02/2013 (ዋልታ) – በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተገነቡ 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው አራት ደረጃቸውን የጠበቁ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገዶች ተመረቁ።
ከዚህም ጎን ለጎን 30 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ተጥሏል፡፡
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ መሀመድ ዩሱፍ ሮብሌ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከዚህ ቀደም እኩል የልማት ተጠቃሚነት አልነበረም።
ክልሉ በራሱ የተፈጥሮ ሀብትና ንብረት የማዘዝ መብቱን ተነጥቆ መቆየቱንን ያስታወሱት ኃላፊው፣ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የክልሉ ህዝብ በልማት ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል ብለዋል።
የጅግጅጋ ከተማ በመልማት ጸጋዋ ልክ እንደ ሌሎች የክልል ከተሞች ምቹና ተመራጭ ለማድረግ የለውጡ አመራር ባደረገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ዛሬ ግንባታው ከሚጀመረው 30 ኪሎ ሜትር መንገድ 7 ኪሎ ሜትሩ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሚሰራ ሲሆን፣ ቀሪው በክልሉ መንግስት በጀት የሚገነባ ነው ተብሏል።
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።