በገቢዎች ሚኒስቴርና በጉምሩክ ኮሚሽን ያልተሰበሰበ ከ9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መኖሩ ተረጋገጠ

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) በገቢዎች ሚኒስቴር ሥር ባሉት 9 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና በጉምሩክ ኮሚሽን ሥር ባሉት 10 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በታክስ ኦዲት እና በ3 መሥሪያ ቤቶች ከውዝፍ ያልተሰበሰበ 9 ቢሊየን 527 ሚሊየን 539 ሺሕ 626 ብር በላይ ገቢ መኖሩን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2013 በጀት ዓመት የኦዲት ክዋኔ ሪፖርትን ለምክር ቤቱ እያቀረበ ይገኛል፡፡

ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በገቢ ግብር፣ ቀረጥ እና ታክስ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብን በሚፈቅዱ አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች መሠረት የመንግሥትን ገቢ የሰበሰቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት መደረጉን ዋና ኦዲተር መሠረት ገልፀዋል።

በዚህም መሠረት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤቶች እና በሥራቸው ባሉ 21 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የንግድ ትርፍ ግብር፣ የገቢ ግብር፣ ቀረጥ እና ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ፣ ቅድመ ግብር እና የአክሲዮን ትርፍ ድርሻ ብር 374 ሚሊየን 159 ሺሕ 232 ብር በላይ እና በሌሎች 32 መሥሪያ ቤቶች ብር 36 ሚሊየን 735 ሺሕ 525 ብር በድምሩ ብር 410 ሚሊየን 894 ሺሕ 758 ብር ገቢ ተሰብስቧል ብለዋል፡፡

በደንቡ መሠረት ገቢ ካልሰበሰቡ መሥሪያ ቤቶች መካከል በጉምሩክ ኮሚሽን የቃልቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ የድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት፣ በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች፣ በባሕር ዳር ገቢዎች ቅ/ጽ/ቤት፣ ምዕራብ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት እና የቅዱስ ጴጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 353 ሚሊየን 7 ሺሕ 609 ብር በላይ የክዋኔ ኦዲት ግኝት መኖሩ ዋና ኦዲተሯ አስታውቀል፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር ሥር ባሉት 9 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና በጉምሩክ ኮሚሽን ሥር ባሉት 10 ቅ/ጽ/ቤቶች በታክስ ኦዲት/በድህረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት እና በ3 መ/ቤቶች ከውዝፍ ያልተሰበሰበ በድምሩ 9 ቢሊየን 527 ሚሊየን 539 ሺሕ 626 ብር በላይ ገቢ መኖሩ መረጋግጡንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ብር 1 ሚሊየን 491 ሺሕ ብር በላይ እና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ 21 ሺሕ 749 ብር በላይ  በድምሩ 1 ሚሊየን 513 ሺሕ 651 ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መገኘቱ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ 632 ሺሕ 44 ብር በላይ ፣ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 241 ሺሕ 244 ብር  እና በቀብሪዴሃር ዩኒቨርስቲ 128 ሺሕ 30 በድምሩ 1ሚሊየን 1መቶ ሺሕ 318 ብር በላይ በክፍያ መመሪያ ከተወሰነው የገንዘብ መጠን በላይ በጥሬ ገንዘብ ወይም በቼክ ወጪ የተደረገ ሒሳብ መገኘቱ በቀረበው ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል በወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለረጅም ዓመታት ሒሳብ ሳይደረግ በባንክ ውስጥ የተጠራቀመ የገቢ ሒሳብ 87 ሚሊየን 909 ሺሕ 298 ብር በላይ መገኘቱ በሪፖርቱ መገለጹን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያሳያል።