በገንዘብ ሚኒስትሩ የተመራ ልዑካን ቡድን ከቢል እና ሜሊናዳ ጌትስ ሊቀመንበር ጋር ተወያየ

ሚያዝያ 16/2014 (ዋልታ) በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራው ልዑካን ቡድን ከቢል እና ሜሊናዳ ጌትስ የጋራ መስራችና ሊቀመንበር ሜሌንዳ ጌትስ ጋር ተወያይቷል።
ልዑካን ቡድኑ ውይይቱን ያደረገው በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም ባንክና የዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የፀደይ ወቅት ስብስባ ጎን ለጎን መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ውይይቱ ቢል እና ሜሊናዳ ጌትስ በኢትዮጵያ በጤና፣ ግብርናና ዲጂታል ዘርፎች እያደረገ ባለው ድጋፍ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል።
የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እ.አ.አ በ2000 የተቋቋመ ዓለም ዐቀፍ የተራድኦ ድርጅት ነው።
ልዑካን ቡድኑ ከስብሰባው ጎን ለጎን የሁለትዮሽና የባለብዙ መድረክ ምክክሮች በማድረግ ላይ እንደሆነ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ላለፉት ስድስት ቀናት በዋሺንግተን ዲሲ ሲካሄድ የነበረው የዓለም ባንክና የዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የፀደይ ወቅት ስብስባ ትናንት ተጠናቋል።