በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ ሴት ነዋሪዎች የምርጫ ስልጠና ተሰጠ

ሚያዝያ 12/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ወጣቶችና ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ ሴት ነዋሪዎች ስለምርጫ አስፈላጊነት ስልጠና ሰጥቷል፡፡

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቀን እየተቃረበ ቢመጣም የምርጫ ካርድ አውጥቶ ይበጀኛል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ከመዘጋጀት አኳያ በመራጩ የህብረተሰብ ክፍል ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ተገልጿል፡፡

የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍም 150 ገደማ የሲቪክ ማህበራት ፍቃድ ወስደው ለመራጩ የህብረተሰብ ክፍል ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ፈቃድ አግኝተው ስልጠና ከሚሰጡ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ወጣቶችና ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ አንዱ ነው፡፡

በአጠቃላይ 30 ሺህ ለሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና መስጠቱን ያስታወቀው ተቋሙ፣ አሁን ላይ ካርድ አውጥቶ ለመምረጥ ያለው ተነሳሽነት አናሳ መሆኑን በመመልከት ሴቶች ካርድ አውጥተው ያሻቸውን እንዲመርጡ ስልጠናውን አዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ቢሮ፣ ሴቶች ይጠቅመኛል ያሉትን ፓርቲ ካርድ በመውሰድ እንዲመርጡ ለማስቻል መስራት ይገባል ነው ያለው፡፡

(በሱራፌል መንግስቴ)