በጋምቤላ ከተማ የጸጥታ ችግር የፈጠሩ ግለሰቦች

ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ

ነሐሴ 28/2013 (ዋልታ) በጋምቤላ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር የተጠረጠሩ 30 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

በከተማዋ  ሽብር ለመፍጠር የተቀነባበረው ሴራ በማክሸፍ የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ተመልሶ ነዋሪው የተለመደውን የዕለት ተዕለት ስራውን እያከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ግለሰቦቹ በአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪነት በከተማው የጸጥታ ችግር ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የተጠረጠሩ ናቸው።

እነዚህ 30 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት።

ተጠርጣሪቹ በጋምቤላ ከተማ ለመፍጠር የሞከሩት ሽብር የህወሓት አሸባሪ ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት የለመደው ሕዝቦችን የማጋጨት ሴራ መሆኑን ጠቁመው፣ ሕዝቡ የቡድኑን ሴራ በማክሸፍ ለክልሉ ሰላም ላሳየው ቁርጠኝነት አመስግነዋል።

በሽብር ቡድኖቹ ተታለው ጫካ በመግባት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።