በጋምቤላ ክልል ለአሸባሪው ሕወሓት ተላላኪ የነበሩ 24 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ

ኅዳር 8/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል የሽብርተኛው ሕወሓት ተላላኪ የሆነውና ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) ብሎ የሚጠራው ድርጅት አባል የነበሩ 24 ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ሰጡ።

ለአሸባሪው ሕወሐትና ሸኔ ተላላኪ በሆነው ጋነግ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በመታለል ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው የነበሩ ሰዎች የቡድኑ ዓላማ አገር ማፍረስ መሆኑን በመገንዘብ በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ሰጥተዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ ቡድኑ ከአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ጋር አገር የማፍረስ ሴራ ነድፎ መንቀሳቀሱን በመቃወም ወጣቶቹ በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል።

በከሰረው በሕወሓት ጁንታና በሸኔ ቡድን የሀሰት ትርክት ተሳስተው  ጫካ ገብተው እንደነበረም  ነው የገለጹት፡፡

ቀሪ ያልተመለሱ የሽፍታው ቡድን አባላትም የመረጡት አማራጭ ስህተት እንደሆነ ተገንዝበው እጃቸውን በመስጠት በክልሉ ውስጥ በሚደረገው የሠላም እና የልማት እንቅስቃሴ ሚናቸውን መጫወት አለባቸው ብለዋል፡፡

የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተመለሱ የቡድኑ ታጣቂዎች በበኩላቸው በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ከትጥቅ ትግል ይልቅ ሠላማዊ መንገድ መከተል ለሁሉም አስፈላጊ መሆኑን መናገራቸውንም ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡