ሐምሌ 18/2013 (ዋልታ) – በጋምቤላ ክልል ላሬ ወረዳ በአራት ቀበሌዎች በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በ4 ሺህ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋትቤል ሙን የጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም ኤጀንሲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የጎርፍ አደጋው የደረሰው ከደጋው ክፍል የሚመጣ ውሃ ሞልቶ በመፍሰሱ መሆኑን ጠቁመው፣ በጉዳቱም በመኖሪያ ቤቶች፣ በሰብልና በእንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል፡፡
የጉዳቱን መጠን ለማጣራትና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ከተለያየ አካላት የተውጣጣ ቡድን ወደ ስፍራው እንደሚላክም አስረድተዋል፡፡
በላሬ ወረዳ በሚገኙት ተንዳር፣ ብሊምኩን፣ ማንጎክ እና ንብንብ ቀበሌዎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ 4 ሺህ የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍል ክፋኛ መጎዳቱ ተገልጿል።
በትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙት የጎርፍ አደጋ ተጎጅዎቹ መልሶ ለመቋቋም የወገን እና መንግስት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መናገራቸውን ከክልሉ የመንግሥት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡