በጋምቤላ ክልል በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ከ16 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቀሉ

ነሀሴ 5/2016 (አዲስ ዋልታ) በጋምቤላ ክልል በ4 ወረዳዎች ላይ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ16 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር አስታወቀ።

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ኃላፊ ጋትቤል ሙን እንዳሉት በሃገሪቱ ደጋማው አካባቢ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በጎግ፣ በላሬ፣ በጆርና በዋንቱዋ ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከስቷል ብለዋል።

የጎርፍ መጥለቅለቅ ከደረሰባቸው አራት ወረዳዎች ውስጥ ከ16 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸዉ መፈናቀላቸዉ ጠቅሰው ተፈናቃዮቹን ለጊዜው ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ መደረጉን ገልፀዋል።

የጎርፍ አደጋው በቤት ውስጥ ያሉ ቁሳቁሶች እንዲሁም በቁም እንስሳትና በሰብል ላይም ጉዳት ማድረሱን አስታውቀዋል።

ለተፈናቃዮቹ ከክልሉ መንግስትና ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት በመነጋገር አፋጣኝ ድጋፍ እየተመቻቸ እንደሚገኝ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡