በጋምቤላ ክልል በጎርፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ተደረገ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል በጎርፍ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ዳቡ ዱቄት ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ያስረከቡት በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የእርሻና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢሳያስ ከበደ ድርጅቱ ድጋፉን ያደረገው በክልሉ በጎርፍ የተፋናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ነው።

በቀጣይም ተፈናቃችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከክልሉ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ኃላፊው ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ በበኩላቸው የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በክልሉ በደረሰው የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመታደግ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በክልሉ በዘንድሮው ዓመት የደረሰው የጎርፍ አደጋ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሌሎች ድርጅቶችም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡