የካቲት 05/2013 (ዋልታ) – በጋምቤላ ክልል የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የሥራ ሠዓት ለውጥ መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፒተር ሆዎ እንደገለጹት፣ የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱና ለስራ አመቺ ባለመሆኑ ከየካቲት 3/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ ጊዜያዊ የመንግስት ሥራ ስዓት ለውጥ ተደርጓል።
በለውጡ መሰረትም ቀደም ሲል በመደበኛው የሥራ ስዓት ከጠዋቱ አንድ ሠዓት እስከ ስድስት ሠዓት ተኩል የነበረው ከአንድ ሠዓት እስከ አምስት ሠዓት ተኩል እንዲሆን ተወስኗል።
እንዲሁም ከሠዓት በኋላ ከዘጠኝ ሠዓት እስከ አስራ አንድ ሠዓት ተኩል የነበረው ከአስር ሠዓት እስከ አስራ ሁለት ሠዓት ተኩል እንዲሆን መወሰኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።
የስራ ሠዓት ለውጡ ወይናደጋ የሆነውን የማጃንግ ዞን እንደማይጨምር የጠቆሙት ኃላፊው፣ የመንግስት ሠራተኞች በተጠቀሰው ጊዜ ወደ ቢሮ በመግባት የተለመደውን ሥራቸውን እንዲያከናኑ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በብሔራዊ ሜትሮዎሎጂ ኤጀንሲ የጋምቤላ ክልል አገልግሎት ማዕከል መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት የክልሉ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 40 ነጥብ 4 ዲግሪ ሴልሽየስ፣ የሌሊቱ ደግሞ 16 ነጥብ 6 ዲግሪ ሴልሽየስ ነው።