በጋምቤላ ክልል የእናቶችና ህፃናት ጤና ማሻሻያ ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ

የካቲት 9/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር የእናቶችና ህፃናት ጤና ማሻሻያ ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ።

ለሥርዓተ-ፆተ እኩልነት የማኅበራዊ ጤና ቁርጠኝነት በሚል የተጀመረው ፕሮጀክቱ በሶስት ዓመት ቆይታው ከ268 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን በጀት ሥረዓተ ምግብ ላይ አተኩሮ በአራት የክልሉ ወረዳዎች እንደሚተገበር ተጠቁሟል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የማኅበረሰብ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት አሁን ካለበት ደረጃ ለማሻሻል የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋራ እየሰሩ እንጀሚገኙ ገልፀዋል።

የእናቶችንና ህፃናት ህመምና ሞት ለመቀነስ ከቤት እስከ ትምህርት ቤት አስፈላጊውን የአመጋገብ ሥርዓት እንዲከተሉ በማስተማርና ክትትል በማድረግ በአዕምሮና የአካል ጥንካሬ ብቃት ያለውና ለሀገር ተስፋ ሰጪ ትውልድ ለማፍራት ሁሉም የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ሮት ጋትዊች በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በሚኖረው የሶስት ዓመት ጊዜ የእናቶችና ህፃናትን ጤና እና አመጋገብ እንዲሁም የጤና እና ሥርዓተ-ፆታ ኢ-ፍትሃዊነትን የሚነኩ ማኅበራዊ ውሳኔዎችን ለማሻሻል የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።

ፕሮጀክቱም በሚመለከታቸው አራት ወረዳዎች እና 79 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ ከ125ሺሕ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ ችግሩ ጎልቶ የወጣባቸው ናቸው ተብለው በተመረጡት በእንደ ዲማ፣ መንገሺ፣ ኢታንግ፣ መኮይ ወረዳዎች ውስጥ 20 ትምህርት ቤቶች፣ 12 ጤና ጣቢያ፣ 3 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እደሚተገበር ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።