በጋምቤላ ክልል የ7 አስፓልት መንገዶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 16/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በጋምቤላ ክልል ከ10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሰባት አስፓልት መንገዶች ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

አስተዳደሩ ለመንገዶቹ ግንባታ ስኬታማነት የጋምቤላ አካባቢ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት መክፈቱን አስታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ ሰለሞን ታደሰ እንደገለጹት አስተዳደሩ በክልሉ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸውን ሰባት የአስፓልት መንገዶች እየገነባ ነው።

በመገንባት ላይ ከሚገኙት መንገዶች መካከል ከጋምቤላ አቦቦ ፑኚዶ፣ ከፑኝዶ ጊሎ ወንዝ፣ ከፑኝዶ ጆር እና ከላሬ ኝንኛንግ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ከእነዚህም መካከል ከአቦቦ ወደ ማጃንግ ዞን የሚወስደው የ76 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ስራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመው ቀሪዎቹ በተለያዩ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ እንደሚኙ ተናግረዋል።

መንገዶቹ ዞኖችን ከክልሉ ማዕከልና ዞኖችን ከወረዳዎች ጋር የሚያገናኙ መሆናቸውን ጠቁመው ግንባታውን በቅርበት በመከታተል በጥራት፣ በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ለማጠናቀቅ በቅርበት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በቀጣይም በክልሉ በአስር ዓመቱ የመንገድ መሰረተ ልማት ስትራቴጂክ እቅድ ስኬታማነት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የመሰረተ ልማት አማካሪ ኡሞድ ኡሞድ እንዳሉት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በክልሉ መከፈት ካሁን በፊት በክልሉ በመንገድ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅርበት መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል።

በጽህፈት ቤቱ መከፈት የክልሉ መንግስት ደስተኛ መሆኑን ጠቅሰው አስተዳደሩ ለጀመራቸው ስራዎች መሳካት ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።