የጋምቤላ ክልል የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እገዛ ያደርጋሉ ያላቸውን የሰለጠኑ 810 የሚሊሻ አባላት አስመረቀ፡፡
የጋምቤላ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ቴንኩዌይ ጆክ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ፣ ሕግ እና ሥርዓት መሬት ላይ ወርዶ እንዲተገበር እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በሥነ ምግባር የታነፀ የፀጥታ ኃይል ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ተመራቂ የሚሊሻ አባላት በሥልጠናው ወቅት ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት በመጠቀም ሕዝብ የጣለባቸውን ሓላፊነት በብቃት እና በታማኝነት ሊወጡ እንደሚገባም ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ መክረዋል።
በክልሉ በጠረፋማ አካባቢዎች የሚደርሰውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጥፋትን ለመከላከል የሚሊሻ አባላት ሠልጥነው ወደ ሥራ መግባታቸው የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያቃልለው እምነታቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት የክልሉን ሕዝብ ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ እና የለውጡን ጉዞ ከዳር ለማድረስ የፀጥታ ኃይሉን አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ሓላፊ አቶ ቶማስ ቱት በበኩላቸው፣ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላት ሚና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል ሲል የጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ዘግቧል።