ሚያዝያ 19/2013 (ዋልታ) – በጋምቤላ ክልል ምርጫ ነክ ግጭቶችን ለመከላከል የሚያስችል 13 አባላት የተካተቱበት ግብርኃይል ተቋቋመ።
በክልሉ በተቋቋመው ግብርኃይል በአባልነት ከተካተቱ መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የሴቶች ፌዴሬሽንና የጸጥታ አካላት ይገኙበታል።
እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ማህበር፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎችና መገናኛ ብዙኃን እንደሚገኙበት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታጠቅ ተፈራ እንደገለጹት፣ ግብርኃይሉን ማቋቋም ያስፈለገው ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የግጭት ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ነው።
ግብርኃይሉ የግጭት ስጋቶች መረጃዎችን አስቀድሞ በመተንተን የመከላከልና ችግሮችም ሲከሰቱ ፈጥነው መፍትሄ እንዳያገኙ የሚሰራ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።