በጋራ የተመዘገቡ ድሎችን ለማፅናት የሚያስችል ምክክር ማካሄዳቸውን የአማራ እና የኦሮሚያ ብልፅግና ፅ/ቤት ኃላፊዎች ገለጹ

ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) በጋራ የተመዘገቡ ድሎችን ለማፅናት እና ፈተናዎችን በወንድማማችነት ለመሻገር የሚያስችል ምክክር ማካሄዳቸውን የአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ገለጹ።

ለዘላቂ ሠላም እና ሁለንተናዊ ብልፅግና በሚል መሪ ቃል በሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የተመራው መድረክ ለሁለት ቀናት በባህርዳር የተካሄደ ሲሆን የአማራ ክልል፣ የዞን እና ወረዳዎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች የተሳተፉበት ነው።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የክልሎቹ የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊዎች ግርማ የሺጥላ እና ፈቃዱ ተሠማ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሠጥተዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ከማምጣት ጀምሮ እስከ ብልፅግና ምስረታ ሀገራዊ ለውጡን ለማፅናት የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች በህዝብ ለህዝብ እና የአመራር ለአመራር ግንኙነቶች የላቀ ሚና መጫወታቸውን አንስተዋል።

መድረኩ ባለፉት ጊዜያት በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ድሎች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና መፍችሄዎች ላይ በመምከር አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን የአማራ ክልል ብሌፅግና ፓርቲ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅ/ፅ/ቤት ሀላፊ ፈቃዱ ተሠማ በበኩላቸው መድረኩ የአመራር አንድነትን የሚያጠናክር ብዥታዎችን የሚያጠራ እና የህዝብለህዝብ ግንኙነትን ማሳደግ የሚያስችል መግባባት የተደረሠበት ነው ብለዋል።

ሁለቱ ህዝቦች በጋራ ለሀገር ብልፅግና እና ለልማት ተሰልፈዋል፤ ለሀገር ክብር በአንድነት ተዋድቀዋል ያሉት ኃላፊው ይህን አንድነት ለማጠናከርና ለህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ለመስራት ውሳኔዎችን አሳልፈናል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።