በግለሰብ ቤት ተከማችቶ የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር ዋለ

መጋቢት 06/2013 (ዋልታ) – የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በግለሰብ ቤት ተከማችቶ የነበረ የጦር መሳሪያን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ ፡፡
በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጭኮ ከተማ አስተዳደር እና በሀዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ የጦር መሳሪያው መያዙን የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጎሳዬ ለገሰ ገልፀዋል ፡፡
በጭኮ ከተማ ላይ በተደረገው ክትትል 30 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ እና ሁለት መትረየስ ተይዟል፡፡
በተመሳሳይ በሀዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ፉራ ቀበሌ ልዩ ቦታው ወልደ አማኑኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉ ልዩ ሀይል በጋራ ባደረጉት ፍተሻ 98 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ከ4 ሺህ 583 መሰል ጥይት ጋር መያዙ ነው የተገለጸው፡፡
እንዲሁም 3 ሺህ 546 የክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ጥይት ከሶስት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል ፡፡