በግብርና ቢሮ ኃላፊ የተመራው ልዑክ በሻሸመኔ ወረዳ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት አስጀመረ

ጥቅምት 3/2015 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አበራ ወርቁ የተመራው የልዑካን ቡድን በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ወረዳ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወይም ኮምፖስት ዝግጅት አስጀመረ።

የልኡካን ቡድኑ ዛሬ በምዕራብ አርሲ ወረዳ ሻሸመኔ ወረዳ ኢቢቻ መንደር ህብረተሰቡ ከአካባቢው ቁሳቁስ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድግ፣ የአፈር ለምነትን ለማሳደግ እና የማዳበሪያ እጥረትን ለመቀነስ ነው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ያስጀመረው።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አበራ ወርቁ የክልሉ መንግስት በአራት ጉዳዮች ላይ ማለትም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ እና የወጪ ንግድ መጨመር ላይ በትኩረት ለመስራት ማቀዱን ገልጸዋል።

ዓላማውም የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ እና የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እንደሆነ በማመላከት እንደ ክልል ባለፈው ዓመት 45 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ኮምፖስት መዘጋጀቱንና በዚህ ዓመት ከ90 እስከ 100 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ኮምፖስት ለማዘጋጀት መታቀዱን ተናግረዋል።

የሀገሪቱን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሕብረተሰቡ መንግስት በሚያደርገው ጥረት በትብብር መስራት እንዳለበትም ገልፀዋል።

የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳዳሪ አህመድ ሀጂ በበኩላቸው ሕብረተሰቡ በከፍተኛ ወጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ማዳበሪያ ለመቀነስ ከተለያዩ ቅሪቶች ማዳበሪያ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።