የካቲት 22/2013 (ዋልታ) – በግብጽ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በግብጽ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር 125ኛውን የአድዋ ድል በዓል ማክበሩን ገለጸ።
በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ የአድዋን ድል ስናከብር አያቶቻችን ታግለው ያቆሟትን አገር ሰላም በማስጠበቅ ወደ እድገትና ብልጽግና ለማሸጋገር የበኩላችንን ሚና በመጫወት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
የአድዋ ድልን በሚመለከት ገለጻ ያደረጉት የሚሲዮኑ ምክትል መሪ አምባሳደር መርዋን በድሪ በበኩላቸው፣ በአድዋ ድል የተመታው የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የዘረኝነት አስተሳሰብም ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ይህ የአያቶቻችን ገድል፣ አሁን የተጋረጡብንን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በአንድነት ለመወጣት የሞራል ስንቅ ይሆናል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያኖች ባሉበት አገር ሆነው የአገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በጽናት እንዲሰሩም ጥሪ መቅረቡን በግብጽ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።