ሚያዚያ 18/2013 (ዋልታ) – በግንባር የተሸነፉት አገር አፍራሽ ኃይሎችና ሌሎች አካላት በዲጂታል ሚዲያ ስም የማጠልሸት፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማቀናበር ህዝብንና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የማሳሳት ስራዎች መስራታቸውን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ገለፁ።
በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢፍጣር መርኃግብር አዘጋጅቷል።
መርሐ-ግብሩን በንግግር የከፈቱት በጂቡቲ የኢፌዲሪ ልዩ-መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በመከላከያ ሰራዊት ላይ በሰሜን ዕዝ በተፈፀመውና ታሪክ ይቅር የማይለው አረመኔያዊ ጥቃት ተከትሎ ህግ የማስከበር እርምጃ መደረጉንና በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን አውስተዋል።
በግንባር የተሸነፉት አገር አፍራሽ ሃይሎችና ሌሎች አካላት በዲጂታል ሚዲያ የተሳሳተ መረጃዎችን በማቀናበር ህዝብንና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የማሳሳት ስራዎች መስራታቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም በውጭ፣ በተለይም በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ እውነታውን በአካልም ሆነ በሳይበር ሚዲያው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አምባሳደር ብርሃኑ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በህዳሴው ግድብ እና በቀጣይ በኢትዮጵያ በሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ዙሪያ ሰፋ ያለ መግለጫ ሰጥተዋል።
በወቅቱም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው፣ ዴሞክራሲን የማስፈንና ሰላምን የማስጠበቅ ኃላፊነት የህዝብም ድርሻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከውጭም ከውስጥም አገርን ለማሸበር ለሚሰሩ እኩይ ኃይሎች አጀንዳ መሳሪያ ላለመሆን አንድነታችንን ማፅናት ይጠበቅብናልም ብለዋል።
ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚንሸራሸሩ መረጃዎችን የማጣራትና ለአገር በሚበጅ መንገድ በኃላፊነት የመጠቀም እንዲሁም እውነታውን በንቃት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማድረስ የዜግነት ግዴታ መሆኑን ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።