በግንባታ ዘርፉ ላይ ያሉ የኢኮኖሚ አሻጥሮች ኢንዱስትሪው እንዲጓተት ማድረጋቸው ተጠቆመ

ጥቅምት 16/2015 (ዋልታ) የሀገራችን የግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲጓተት ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል በግንባታ እቃዎች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ መናር ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል።

በተለይም አሁን ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሲሚንቶ ዋጋ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በጊዜ ተገንብተው እንዳይጠናቀቁ ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡

ሌላው ለግንባታ ዘርፉ መሰናክል ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ለግንባታ በሚያስፈልጉ እቃዎች ላይ የሚሰራው የኢኮኖሚ አሻጥር ተጠቃሽ ነው።

የሲሚንቶ ዋጋ እንዲንር በሚሰራው የኢኮኖሚ አሻጥር የተነሳ በሀገራችን የግንባታ ኢንዱስትሪ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳረፈ ነው የሚነገረው፡፡

በአገር ደረጃ እየተሰራ ባለው የኢኮኖሚ አሻጥር ሳቢያ ከፍተኛ የሆኑ የመንግስት ፕሮጀክቶች ሳይቀሩ ተፅዕኖ እንደደረሰባቸውም ይጠቀሳል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በዘርፉ ላይ ያሉ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ለመቀነስ የግንባታ እቃዎች ላይ ያለውን የምርት ሂደት ማሳደግ እንደሚገባ ቆይታቸውን ከዋልታ ጋር ያደረጉ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር አመራሮች ተናግረዋል።

በግንባታ እቃዎች ላይ የሚሰራውን የማጭበርበር ድርጊት ለመቀነስ ከህብረተሰቡና የፀጥታ አካላት ጋር በትብብር መስራት ይኖርባቸዋል የሚሉት በዘርፉ ላይ የተሰማሩት ግርማ ሀብተማርያም በህገወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

በግንባታ እቃዎች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት በመቀነስ በግንባታ እቃዎች  ላይ የሚታየውን የዋጋ አለመረጋጋት ለመቅረፍ  ትኩረት ሰጥቶ መስራት  እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ዋና ፀሀፊ ሰለሞን አለማየሁ ናቸው።

የግንባታ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገር እድገት የሚያበረክተው አስተዋፆኦ ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉትን ችግሮችን ለመፍታት በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

በሱራፌል መንግስቴ