ሚያዚያ 24/2016 (አዲስ ዋልታ) በግንቦት ወር የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት በልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
በግንቦት የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ተመላክቷል።
በእነዚህ ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ስፍራዎች ላይ ለዝናብ መፈጠር አመቺ የሆኑ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች አንጻራዊ ጥንካሬ እንደሚኖራቸውና በተለይም የምድር ወገብን አቋርጦ ወደ ሀገራችን የሚገባው ዕርጥበት አዘል የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ የተሻለ የደመናና የዝናብ ሥርጭት በደቡባዊው አጋማሽ፣ በመካከለኛው እና በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የትንበያ መረጃዎች ያሳያል ተብሏል፡፡
በደቡብ፣ በደቡብ ምስራቅ፣ በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅ፣ በመካከለኛው፣ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ጥንካሬ ይኖራቸዋል፡፡
በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ አመላክቷል፡፡
በደቡብ፣ በደቡብ ምስራቅ፣ መካከለኛው፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቅጸበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአፋር ክልል፣ ሀረር፣ ድሬዳዎ፣ የሶማሌ ክልል ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በምስራቅ አማራ አካባቢዎች ከሚኖረው ከባድ መጠን ያለው ዝናብ በመነሳት ቅጸበታዊ ጎርፍ የማስከተል አቅም ስለሚኖረው ከወዲሁ ማህበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።