በጎንደር ከተማ የማኅበረሰብ ንቅናቄና የገቢ ማሰባሰቢያ

ነሐሴ 29/2013 (ዋልታ) – በአሸባሪው ትሕነግ ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም የማኅበረሰብ ንቅናቄና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።
መርሃ ግብሩ ወራሪው ኃይል ጦርነት በከፈተባቸው አካባቢዎች ያለውን የጦርነቱን አሁናዊ ሁኔታ ማሳወቅ፣ የጉዳቱን መጠን መመዘን፣ የማኅበረሰብ ንቅናቄን መፍጠር እንዲሁም ሃብትና ንብረታቸው ለወደመባቸውና ከቤታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ሕዝቡ አለኝታነቱን እንዲያሳይ ማድረግ የሁነቱ ዓላማ እንደሆነ ነው የተገለጸው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደ ወይን (ዶ/ር) አሸባሪው ቡድን በሕዝብ ትግል ከሥልጣን ከወረደ በኋላም ይሁን በሥልጣን ላይ እያለ የተለያዩ ግፎችን የሚፈጽም እና አገር በማተራመስ እኩይ ዓላማ የተጠመደ መሆኑን አስረድተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ መለገሱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ለኅልውና ዘመቻው የሚሆን 54 ሚሊዮን ብር በላይ እያሰባሰበ እንደሚገኝ አሳውቀዋል።
የሽብር ቡድኑ እየፈጸመ ያለው ወረራና ኢትዮጵያን ለማተራመስ እያካሄደ ያለውን ድርጊት ለማስቆም ሕዝቡ ሁሉን ዐቀፍ ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና አማካሪ ደሳለኝ አስራደ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው ወራሪው ቡድን የአማራን ሥነ ልቦና ለማዳከምና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየጣረ የሚገኝ ቢሆንም የሕዝቡን አንድነት እና መተባበር ሊሰብረው አይችልም፤ በተባበረ ክንድ የተጎዱ አካባቢዎችን ጠግኖ ለወገን መድረስ ይገባል ማለታቸውን ከአሚኮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።