በጤናው ዘርፍ ሲተገበር የቆየው “ዳጉ” ፕሮጀክት ውጤት አስገኝቷል

ጥቅምት 9/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል ላለፉት አምስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው “ዳጉ” ፕሮጀክት ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ፕሮጀክቱን የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የለንደኑ ስኩል ኦፍ ሃይጂን እና ትሮፒካል ሜዲሲን በጋራ በመሆን ላለፉት አምስት ዓመታት ሲተገብሩት ቆይተዋል።

በፕሮጀክቱ ጎንደር፣ ሀዋሳ፣ ጅማ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ስራዎች ላይ ተሳትፈዋል።

የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ፤ “ዳጉ “ፕሮጀክት ውጤታማ መሆኑን አብራርተዋል።

በፕሮጀክቱ ከአቅም ግንባታ አኳያ 10 ተማሪዎች የሦስተኛ ዲግሪ እንዲማሩ መደረጉን ገልጸዋል።

በአራት ክልልሎች የእናቶችና ህጻናት ጤና የመጀመሪያው ጤና ኤክስቴንሽን ውጤታማነት በፕሮጀክቱ ጥናትና ምርምር ግምገማ መካሄዱንም ዶክተር ጌታቸው ተናግረዋል።

በጤና ኤክስቴሽን አተገባበሩ እና ወደ ፊት በተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ምን ሊሰራ ይገባል? የሚለውም ተዳስሷል ነው ያሉት።

በፕሮጀክቱ እስካሁን 20 የጥናትና ምርምር ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ “በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው የጤናው ዘርፍ ገጾች ላይ ወጥተዋል” ብለዋል።

በጥናቱ የተገኙ በተለይም ለጤና ኤክስቴሽን ስራዎች ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን ወስዶ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

“ከዚህ በፊት ለጤና ስርዓት ማጣቀሻ መረጃ በአብዛኛው የውጭ አገር ህትመቶችን እንጠቀም ነበር” ያሉት ዶክተር ጌታቸው፤ ፕሮጀክቱ የአገሪቷን የጤና ስርዓት የዳሰሰ በመሆኑ ትክክለኛ መረጃ እንደተገኘበት ገልጸዋል።

በኢንስቲትዩቱ የስርዓተ ጤና እና ስነ ተዋልዶ ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ ጌታቸው፤ ፕሮጀክቱ በደቡብ፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት አሰጣጥን እንደዳሰሰ ገልጸዋል።

“በተለይም የእናቶችና ህጻናት ጤና ተደራሽነት ላይ የበለጠ ስራ የሚፈልግ መሆኑ በዚሁ ፕሮጀክት ተለይቷል” ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ ቢል ኤንድ ሚሊኒዳ ጌትስ ፋውንዴሽን 1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ተጠቁሟል።