በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተጠቆመ

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ገለጹ፡፡

ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ናይጀሪያና ኬንያ የተሳካ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በናይጄሪያ በነበራቸው ጉብኝት ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት መሃመዱ ቡሃሪ ጋር  የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረጉ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2021 ሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ 2022 ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ጥሬ ብር ወደ ትግራይ ክልል መላኩን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም 87 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሰብዓዊ እርዳታ ምግብ እና ከ783 ሺሕ ሊትር በላይ ነዳጅ መላኩን አብራርተዋል፡፡

በተጠቀሱት ጊዜያት 217 ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ የህክምና መድኃኒቶች እንዲሁም የመጠለያ ግብዓቶች ጨምሮ 130 ሺሕ ኪሎ ግራም ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድጋፎች ተልከዋል ነው ያሉት፡፡

አሸባሪው ሕወሓት ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ሕዝቡን በኃይል ለጦርነት እየመለመለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ድርጊቱ ቀጣዩን የእርሻ ሥራ እንደሚያደናቅፍ እና በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያባብስ አመላክተዋል፡፡