በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው 536 የጤና ተቋማት 463ቱ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ

ዶ/ር ሊያ ታደሰ

ነሐሴ 15/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው የሕወሓት ወረራ በአፋር እና አማራ ክልሎች ጉዳት ከደረሰባቸው 536 ጤና ተቋማት ውስጥ 463 የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከዚህ ውስጥ 319 ጤና ተቋማት በከፊል አገልግሎት የጀመሩ እና ወደ ተሟላ አገልግሎት ለመመለስ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቁ መሆናቸውንም ጠቁሟል።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት ውስጥ የጤና ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።

ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ሚኒስቴሩ የተለያዩ የድንገተኛ ምላሽ ሥራዎችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።

ይህን ለማስተግበር ዕቅድ ተዘጋጅቶ እንደ ሴክተር እና ከሌሎችም ሴክተሮች ጋር በገንዘብ ሚኒስቴር በሚመራ የተጀመሩ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል ከተጎዱት 40 ሆስፒታሎች እና 453 ጤና ጣቢያዎች 10 ሆስፒታሎች እና 134 ጤና ጣቢያዎች ወደ ሙሉ አገልግሎት መመለሳቸውን ጠቅሰው 25 ሆስፒታሎች እና 273 ጤና ጣቢያዎች ደግሞ ከፊል አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ በርካታ ጤና ኬላዎች በመልሶ ግንባታ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰው አምስት ሆስፒታሎች እና 46 ጤና ጣቢያዎች አሁንም ድረስ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

በአፋር ክልል ጉዳት ከደረሰባቸው ሁለት ሆስፒታሎች እና 41 ጤና ጣቢያዎችም አንድ ሆስፒታል እና 20 ጤና ጣቢያዎች ታድሰው በከፊል አገልግሎት መጀመራቸውን አመልክተው አንድ ሆስፒታል እና 21 ጤና ጣቢያዎች እስካሁን ወደ ሥራ መመለስ አልተቻለም።

በሁለቱም ክልሎች ወደ ሥራ ያልገቡ ቀሪዎችን ተቋማት ወደ ሥራ ለመመለስ የፀጥታ ችግር እንቅፋት መሆኑንም ገልጸዋል።

ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከፌዴራል ሆስፒታሎች፣ ኤምባሲዎች፣ ከልማት አጋር ድርጅቶች፣ ዳያስፖራዎች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመተባበር በተሠራው ሥራ መሠረታዊ እና ሕይወት አድን የሆኑ ጤና አገልግሎቶች በግጭቱ በተጎዱ ጤና ተቋማት ውስጥ ማስጀመር ተችሏል ብለዋል።

እስካሁን ድረስ ከባለድርሻ አካላት በግብአት፣ በመሣሪያ በገንዘብ 600 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት መሰብሰቡንም መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

እስካሁን ድረስ በግለሰብና ተቋም ደረጃ እገዛ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበው በርካታ ጤና ተቋማት ወደ ሥራ መመለሳቸው አበረታች ቢሆንም ሁሉም ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ ስለሚጠይቅ አሁንም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!