በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

መጋቢት 17/2014 (ዋልታ) የኦሃዩ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአማራና በአፋር ክልል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በኦሃዩ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ ድርጅት የቴክኒካል ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ለጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ አስረክበዋል።

ዶክተር ኤባ በዚሁ ጊዜ ድርጅቱ ከ10 ዓመታት በላይ ለጤና ሴክተሩ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ 18 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ቀርፆ የጤና ሴክተሩን የመደገፍ ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተደረገውም ድጋፍ የዚሁ ድጋፍ አካል መሆኑን ገልጸው በአማራና አፋር ክልል ለሚገኙ አምስት ሆስፒታሎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዙ መሣሪያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ድጋፉ ከማይክሮስኮፕ ጀምሮ ጤና ተቋማቱ እጅግ የሚያስፈልጋቸው የዘመናዊ የላብራቶሪ ማሽነሪዎችንና የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ያካተተ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ጎን ለጎንም በሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማቃለል የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው በጦርነቱ በተለይ በሰሜኑ ክፍል ባሉ የጤና ተቋማት ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህንም የጤና ተቋማት መልሶ ለማደራጀት በመንግሥት አቅም ብቻ ማከናወን እንደማይቻል ገልጸው ድርጅቱ ይህንን በመረዳት ያደረገው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በቀጣይም እነዚህን ተቋማት ወደነበሩበት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ከመንግሥት ጎን ሆነው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፉ የተደረገው በአማራ ክልል ለሚገኙት አጣዬ፣  ኃይቅ፣  ኮምቦልቻና ወልዲያ  ሆስፒታሎች እንዲሁም በአፋር ክልል ለሚገኘው ከልዋ ሆስፒታል ነው።