በጫኝና አውራጆች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንዲሰራ ለፖሊስ አመራሮች መመሪያ ተሰጠ

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች ከጫኝና አውራጆች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንዲሰራ ለፖሊስ አመራሮች የስራ መመሪያ መሰጠቱን የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በመዲናዋ በጫኝና አውራጅነት ሥራ ላይ የተደራጁ ማህበራት ለከተማው ሕብረተሰብ ሰላምና ፀጥታ አስተዋጽኦ ማድረግ በሚችሉበት እና አቅምን ያላገናዘበ ክፍያ በመጠየቅ እና በማስፈራራት ህብረተሰቡን በሚያማርሩ ጫኝና አውራጆች ላይ ህጋዊ እርምጃ በሚወሰድበት ሁኔታ ላይ በከተማ ደረጃ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግም ወደ ህግ ማስከበር ስራው ለመግባት ዛሬ ለፖሊስ አመራሮች የስራ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዳይሬክተር ኮማንደር ሰለሞን ፋንታሁን በህጋዊና ህገ-ወጥ መንገድ የተደራጁ አንዳንድ ጫኝና አውራጆች ዕቃ ለመጫን እና ለማውረድ አቅምን ያላገናዘበ ክፍያ በመጠየቅ ህዝብን እያማረሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ የህዝብ ቅሬታ እና አቤቱታ የሚበዛባቸው ጉዳዮችን በመለየት ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ በመድረኩ ላይ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር መንገሻ ሞላ በሰጡት የስራ መመሪያ የፖሊስ ዋናው ተልዕኮ ህግን የማስከበርና ህዝብን የሚጎዱ ሀይሎችን በመቆጣጠር በህግ አግባብ እንዲጠየቁ ማድረግ በመሆኑ ከማንኛውም ወገንተኝነት ገለልተኛ ሆነን ማገልገል አለብን ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም በጫኝና አውራጅነት ሰበብ ተደራጅተው ህዝብን የሚያማርሩ ማህበራት ቢኖሩም ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ወንጀልን የሚከላከሉና ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ማህበራት መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን ማህበራት በመደገፍ ህገ- ወጥ ድርጊት የሚፈፅሙትን ደግሞ በህግ አግባብ እንዲጠየቁ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡