በፍትህ ሥርዓት የሚስተዋለውን ክፍተት ለማሻሻል ወጥና ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ተገለፀ

የካቲት 9/2014 (ዋልታ) በፍትህ ሥርዓት የሚስተዋለውን ክፍተት ለማሻሻል ወጥና ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ወጥና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት ለማስቻል የፌዴራልና የክልል ጠቅላይ አቃብያነ ህጎች ውይይት በአዳማ ከተማ እያደረጉ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የቀጣይ አምስት ዓመታት የሥራ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ገለፃ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በሰጡት ገለፃም የፌዴራልና የክልል የፍትህ አካላት ተቋሞቻቸውንና የህግ አሰራራቸውን የተሻሉና የተናበቡ በማድረግ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በተለይ ሀገር በቀል ኢ-መደበኛ የማኅበረሰብ ዐቀፍ የፍትህ አገልግሎትን ከመደበኛው የፍትህ ተቋማት አሰራር ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባም ገልጸዋል።

በቅርቡ ይፋ በሆነ አንድ ጥናት ላይ በአገሪቱ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ከፍትህ ጋር በተያያዘ ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን እንደሚያመለክትና ከ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 17 በመቶ የሚሆኑት ጉዳያቸው የሚፈታው በመደበኛው የፍትህ ተቋማት ሲሆን ቀሪ አብዛኛው ሕዝብ ጉዳዩን የሚፈታው መደበኛ ባልሆነው ባህላዊ የህግ አፈታት እንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል ተብሏል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ባህላዊ የፍትህ አሰራሮችን ከመደበኛው የፍትህ ተቋማት ጋር ማስተሳሰር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ አቅጣጫ ተሰጥቷል።

ደምሰው በነበሩ (ከአዳማ)