ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) – በ2013 በጀት ዓመት 290 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ279 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው አስታወቁ፡፡
በዚህም የበጀት አመቱ እቅድ 96 ነጥብ 2 በመቶ የተሳካ ሲሆን፣ የገቢ አፈጻጸሙ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ እቅድ አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በሀገር ውስጥ ታክስ የ29 ነጥብ 6 በመቶ፣ በጉምሩክ የ7 ነጥብ 2 በመቶ በድምሩ የ19 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ወይንም የ45 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የእቅድ አፈጻጸሙ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና የትግራይ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ያሉ ችግሮች ባሉበት የተገኘ በመሆኑ አበረታች መሆኑን አቶ ላቀ አያሌው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡