በ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር ዐቀፍ ፈተና ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በዚህ ዓመት እንዲፈተኑ ተወሰነ

ሚያዝያ 10/2014 (ዋልታ) በጦርነትና ግጭት ውስጥ ሆነው የተፈተኑና የማለፊያ ነጥብ ያላመጡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከ2014 ዓ.ም መደበኛ ተፈታኞች ጋር እንዲፈተኑ መወሰኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና እርማት በተመለከተ ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።

ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውይይት በማድረግ ተጨማሪ የቅበላ አቅም እንዲኖር ከስምምነት ላይ መደረሱን እና ተጨማሪ የቅበላ አቅም በፍትሐዊነት በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ክልሎች እንዲከፋፈል ውሳኔ ተላልፏል።

በሌላ በኩል የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባወጣው መግለጫ የመጀመሪያው ውሳኔ ከዚህ በፊት በተላለፈው የመቁረጫ ነጥብ መሰረት ወደ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች መግባት ከቻሉት የክልሉ ተማሪዎች በተጨማሪ 4 ሺሕ 339 ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቅበላ የሚያገኙ እንደሚሆን አስታውቋል።

የፈተና ውጤት ማሳወቅን በተመለከተም በሁለት ዙር ፈተና በመሰጠቱ አጋጥሞ የነበረው ችግር መታረሙን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ተፈታኞች በስነ-ዜጋ ትምህርት ካጋጠመው ችግር ውጪ ሌላ ችግሮች ባለማጋጠሙ የሌሎች ትምህርት ዓይነቶችን ውጤት ውድቅ ለማድረግ አሳማኝ የውጤት ትንተና አለመኖሩ ተነግሯል።

በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቅበላ የሚያገኙትን ተማሪዎች በተመለከተ በቀደሙት ዓመታት ከመሰናዶ ትምህርት በኋላ ከሚፈተኑ ተማሪዎች ጋር በማነፃፀር የተፈጠረ አለመረዳት መኖሩንም ተጠቁሟል፡፡