ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – በ2020 ኦሮሚያን ከባህላዊ ጎጂ ልምዶች ነፃ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ህፃናት፣ሴቶች እና ወጣቶች ቢሮ ገለፀ ።
ቢሮው የ2013 በጀት አመት ስራን እና በቀጣይ አመት እቅድ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነዉ።
ቢሮው በክልሉ በዚህ አመት በተሰራው ስራ ከ2.1 ሚሊዮን ህፃናት በዘላቂነት እንዲደገፉ ማድረጉ የዚህ አመት ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ባህላዊ ጎጂ ልማዶችን ለማስቀረት በተሰራዉ ስራ በኦሮሚያ ካሉት 7 ሺህ ቀበሌዎች ዉስጥ እስካሁን ከ 1500 በላይ ከባህላዊ ጎጂ ልማዶች ነፃ ማድረግ መቻሉን የኦሮሚያ ህፃናት፣ሴቶች እና ወጣቶች ቢሮ ሃላፊ ሰዓዳ ኡስማን ገልፀዋል ።
ቢሮው ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በሰራዉ ስራ በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለፁት ሃላፊዋ ይህ ተግባርም ማሳያ በመሆኑ ሌሎች ክልሎች ከዚህ ልምድ በመዉሰድ ላይ ናቸዉ ብለዋል።
በመንግስት ተቋማት የወላድ ሴቶች ህፃናት መቆያ ላይ አጥጋቢ ባለመሆኑ ቢሮዉ በቀጣይ አመት በትኩረት ሊሰራበት ማቀዱንም አንስተዋል ።
ቢሮዉ ግምገማና የእቅድ ምክክር መድረኩን በበጀት አመቱ የላቀ የስራ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የዞን እና ከተማ አስተዳደሮች ፅ/ቤቶች እዉቅና እና ሽልማት በመስጠት አጠናቋል ።
(በሶሬቻ ቀበኔቻ)