ሐምሌ 30/2013(ዋልታ) – በሁሉም ክልሎች በ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ መሰረታዊ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ መደረጉን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ የዋጋ ውድነቱን ለመፍታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በተመለከተ መንግስት በድጎማ የሚያቀርባቸውን መሰረታዊ ሸቀጦች ከራሱ ምንጭ የውጭ ምንዛሬ በመመደብና የውጭ ምንዛሬ ባላቸው ባለሃብቶች ከታክስና ከግብር ነጻ ሆኖ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ እንደሚገኝ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም ዘይት፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ የህጻናት የዱቄት ወተት አቅርቦት በሃገር ውስጥ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ሰብል አምራች አርሶ አደሮች፣ የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖችን በማስተሳሰር በሁሉም ክልሎች 14 ሚሊየን ኩንታል በመግዛት በተመጣጣኝ ዋጋ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ ተደርጓል።