በ5 ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃ ማዕከል ሥራ ጀመረ

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) በ5 የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃ ማዕከል የዲጂታል አሰራር ተመርቆ ሥራ ጀመረ።

ማዕከሉ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን አዲሱን የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ጨምሮ ኮቪድ-19፣ ቢጫ ወባ፣ ኮሌራ እና ጊኒ ወርም ዙሪያ የኅብረተሰብ ጤና መረጃዎችን የሚሰጥ ነው።

8335 ላይ ነፃ አገልግሎት የሚሰጠው ብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት መረጃ ማዕከሉ አስተማማኝ የቀድሞ ማስጠንቀቅ፣ የምርመራ እና የክትትል መረጃዎችን ይሰጣልም ነው የተባለው።

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የዲጂታል አገልግሎት ሥርዓቱ ጊዜውን የጠበቀ እና አስተማማኝ የኅብረተሰብ ጤና መረጃ በመስጠትና ጥቆማዎችን በመቀበል ኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሻሽል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የዲጂታል አገልግሎቱ በርካታ ደንበኞችን በአንድ ጊዜ ማስተናገዱ፣ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አውቶሜትድ ማድረጉ፣ ጥቆማዎችን መቀበል ማስቻሉ እና በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠቱ የጤናውን ዘርፍ ዲጂታላይዜሽን ያሻሽለዋል ብለዋል።
የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ኃላፊ ሳሙኤል ያለው ከዚህ ዲጂታል ፕላትፎርም የሚገኙት ትምህርቶች የተለያዩ ዘርፎች ላይ ለምንሰራው የዲጂታል ሥራ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዲጂታል ፕላትፎርሙ ድምጽ እና የጽሑፍ መልዕክትን አቀናጅቶ የሚጠቀም እና በተለይም ደግሞ የኅብረተሰብ ጤና ስጋቶች በሚፈጠሩባቸው አስቸኳይ ጊዜያት ብዛት ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያዳርስ መሆኑን ከኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።