በ5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የታዳሽ የብረታ ብረት ፋብሪካ ተመረቀ

ሰኔ 4/2014 (ዋልታ) በቀን 450 ቶን ብረት የማቅለጥና 600 ቶን ፌሮ ብረት የማምረት አቅም ያለው ታዳሽ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በ5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተገነባው የብረታብረት ኢንዱስትሪው በዱከም ከተማ 50 ሺሕ ካሬ መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ለ700 ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

የፋብሪካው ግንባታ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ እድል ከመፍጠር በዘለለ ለሀገር ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ተጠቁሟል።

አካባቢውን ከብክለት ለመጠበቅም ፋብሪካው በ180 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ ዓለም ዐቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሳሪያ ተገጥሞለታል ተብሏል።

የፋብሪካው ባለቤት ክብሩይስፋው ተክሉ በብረታ ብረት ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለ25 ዓመታት ሰርተዋል።

መስከረም ቸርነት (ከዱከም)