ሐምሌ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮ ቴሌኮም በ6ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 50 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ግማሽ ሚሊዮን ችግኞችን እንደሚተክሉ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ፡፡
“ለአረንጓዴ ኢትዮጵያ የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል ተቋማዊ መሪ ቃል እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞችን በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ወደ 700 መዳረሻዎች መተከሉን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
በዚህም 20 ሺህ ግዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አንስተው በዘንድሮ ዓመትም 4 ሺህ ተጨማሪ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር አስታውቀዋል።
ዛሬ በተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ በአራት አከባቢዎች እንዲሁም በመቀሌ፣ በሀዋሳ፣ በአዳማ እና በነቀምት በተመሳሳይ ሰዓት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ተቋሙ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከዛሬ ሀምሌ 11 እስከ 30 ድረስ በመላው ሀገሪቱ እንደሚያከናውን ተጠቅሷል።
ሚኪያስ ዓለሙ