በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚነሱ ክርክሮች ካሉ ለማስተናገድ ፍርድ ቤቶች ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚነሱ ክርክሮች ካሉ ለማስተናገድ ፍርድ ቤቶች ዝግጁ መሆናቸውን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ አስታውቀዋል።

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከ2014 እስከ 2018 በጀት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ላይ ከፌዴራልና ክልል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ የፖሊስና ወታደራዊ ፍርድ ቤት፣ የማረሚያ ቤት፣ የሕግ ባለሙያዎችና ሌሎች የፍትሕ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሶስት ግቦች በማስቀመጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው አንደኛው ግብ የዳኝነት ነፃነት፣ ገለልተኝነትና ተጠያቂነት ሲሆን ሁለተኛው የዳኝነት ቅልጥፍና ተደራሽነት ነው ብለዋል፡፡

ሶስተኛው ግብ ለዳኝነት አገልግሎት አስተዳደራዊ ድጋፎችን ማጠናከር መሆኑን አንስተው፤ በነዚህ ግቦች ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

“ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ የሚተገበረው ስትራቴጂክ ዕቅድም እነዚህን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል” ብለዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታትን የዳኝነት ነፃነትና ተጠያቂነት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ “ይህም የሕግ የበላይነትን፣ የመንግስትን ቅቡልነት ያስተናግዳል፤ ኢንቨስትመንትን ያበረታታል” ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ፍርድ ቤቶች በነፃነት እየሰሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በፍርድ ቤቶች እየተተገበረ ያለው ማሻሻያ ዋና ዓላማ ፍርድ ቤቶች በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት እንዲያተረፉ ማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቶች ጥቂት ቀናት የቀረውን 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ ለሚመጡ ክርክሮች ፍርድ ቤቶች ዝግጁ መሆኑን ገልፀው፤ ፍርድ ቤቶች ብቁ ውሳኔ ሰጭ ሆነው እንደሚያገለገሉ አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

መንግስት፣ ፓርቲዎችና ህዝቡም በፍርድ ቤቶች ላይ ተቋማዊ እምነት እንዲያሳድሩም አስገንዝበዋል።