በ8 ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 52 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

መጋቢት 27/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 52 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስተኛ መደበኛ ጉባኤው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የስምንት ወራት እቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።

ለምክር ቤቱ የአፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ ባለፉት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 52 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በተጠቀሰው ወራት ከዘርፉ 2 ነጥብ 77 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው ከእቅዱ 91 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

ከግብርናው 1 ነጥብ 75 ቢሊየን፣ ከኢንዱስትሪ ዘርፉ 320 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር፣ ከማዕድን ዘርፍ 389 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ተጨምረውበት በድምሩ 2 ነጥብ 52 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

ገቢው ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡